Wednesday, 28 February 2024

ስንተባበር ታሪክ ሰርተናል፤ እንሰራለንም!

 ስንተባበር ታሪክ ሰርተናል፤ እንሰራለንም!




ከውይይት ይልቅ ጦርነትን የማስቀደምን ኋላቀር አስተሳሰብ ብዙ አገራት ታሪክ አድርገውታል። አንዳንዶች ካሳለፉት ታሪክ ተምረው ሌሎቹ ደግሞ ከሌሎቹ ትምህርት ወስደው ላለመገዳደል ተማምለዋል። 


የማሰብና የማሰላሰል ህሊና እያላቸው ከእንስሳት በታች ወርደው ወንድም ወንድሙን በመግደል የሚመፃደቁ፣ መግደል መሸነፍ መሆኑን የማይረዱ ቡድኖች ያሉባቸው አገራት ደግሞ ጦርነትን ታሪክ ማድረግ ባለመቻላቸው ፈራርሰው ታሪክ ሆነዋል።


በየአገሩ ያሉ አሸናፊ ሀሳብ የሌላቸው ጦር ሰባቂዎች ጭምር የሚረዱት እውነታ በንፁሀን መስዋዕትነት ሀብትን የማገባስ ጊዜአዊ የፖለቲካ ፍጆታ እንጅ ጦርነት ትናንትም ሆነ ዛሬ ነገም ወደፊትም የሚፈታው ችግር አለመኖሩን ነው።


ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ቱባ ባህላዊና ሀይማኖታዊ እሴቶች ያሏት ኢትዮጵያ የውይይት ባህል ባለመዳበሩ እንጅ በንግግር የማይፈታ አንዳች ችግር አለመኖሩን በመገንዘብ ፓርቲያችን ለትብብርና ለፉክክር ፖለቲካ ይተጋል።


የውይይትን ባህልን ለማዳበር አገር በቀል እውቀቶችን ከዴሞክራሲያዊ መርሆች ጋር በማቀናጀት ለመጠቀም ከሚደረገው ጥረት ባሻገር መሰረቱን ለማፅናት ነፃ እና ገለልተኛ ተቋማትን መገንባት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።

 

የኛ ትውልድ የህዝባችንን ህይወት የመቀየር እና ኢትዮጵያን ወደተሻለ ደረጃ የማሻገር ሀላፊነት ያለበት የተንከባለለ ዕዳ ከፋይ ጭምር ነው።


ብርቱ ስንሆን ኢትዮጵያን ለወዳጅነትና ለሽርክና የሚፈልጋት ብዙ ነው። ስንደክም ግን ደካሞች ጭምር ውክልና ተሰጥቷቸው ይጎነትሏታል።


ዓለም አንድ መንደር በሆነችበትና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ከሉዓላዊ አገራት የገዘፈ ፈርጣማ ጡንቻ በያዙበት በዚህ ዘመን የውጭ ተፅዕኖ ቀላል ባይሆንም የአገራት አስተማማኝ ሰላም፣ ዕድገትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት የሚወሰነው በውስጥ አቅም ነው።


አገራችን በቅርቡ ገብታበት ከነበረው ውስጣዊ ፈተና እና ውጫዊ ጫና በድል ተሻግራ ብሪክስን ከመሰለ ተፅዕኖ ፈጣሪ ስብስብ አባል የሆነችው፣ በቅርቡም ከሶማሌላንድ ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ ወደብ ለማግኘት እየተደረገ ያለው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ ተጨባጭ ጥንካሬዋንና የወደፊት ተስፋዋን አመላካች ነው።


ዲፕሎማሲያችን ወይም አጠቃላይ የውጭ ግንኙነታችን ውስጣችን ሲደክም የሚዳከም ስንጠነክር ደግሞ የሚጠነክር በመሆኑ ቁልፉ በእጃችን ነው።


ያለችን አንዲት አገር ናት፤ አንድ አይን ያለው በአፈር አይጫወትም እንዲሉ አበው መቼም ይሁን የትም ማንም ኢትዮጵያን ለድርድር ማቅረብ አይገባም። ሲመቸን የምንወዳት ሳይመቸን የምንረግማት ሳይሆን የከፍታዋም የዝቅታዋም ምክንያት እራሳችን መሆናችንን ተረድተን ድህነቷን ቀርፈን ብልፅግናዋን ለማረጋገጥ ታሪካዊ አሻራችንን እናሳርፍ!


#prosperity 

No comments:

Post a Comment

<script async src="https://pagead2.googlesyndication.com/pagead/js/adsbygoogle.js?client=ca-pub-8211633838377135" crossori...