Sunday, 8 January 2023

አፋሮች ከኢትዮጵያ አልፈው የቀጣናው ትስስር እንዲጠናከር የሚሰሩ ሕዝቦች ናቸው” መሃሪ መአሾ (ሻለቃ) የቀድሞ የትግራይና የወሎ ክፍለ አገሮች ምክትል አስተዳዳሪ

አፋሮች ከኢትዮጵያ አንድነት አልፈው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ትስስር እንዲጠናከር አበክረው የሚሰሩ ሕዝቦች ናቸው ሲሉ የቀድሞ የትግራይ ተቀዳሚና የወሎ ክፍለ አገሮች ምክትል አስተዳዳሪና የኤርትራ ጉዳይ ልዩ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር መሃሪ መአሾ (ሻለቃ) ገለጹ።መሃሪ መአሾ (ሻለቃ) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አፋሮች ለኢትዮጵያ አንድነት የታገሉና ለምስራቅ አፍሪካ ሕዝቦች ትስስር መጎልበት ከፍተኛ ሚና የሚወጡ ሕዝቦች በመሆናቸው አስፈላጊው ዕውቅናና ክብር ይገባቸዋል።አፋር ካለው መልከአምድራዊ አቀማመጥ አኳያ በታሪኩ ከብዙ የውጭ ወራሪዎች ጥቃት ደርሶበታል። ይሁንና ጥቃቶቹን በመመከት የኢትዮጵያን አንድነት እንዲሁም ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ረገድ ሰፊ ተጋድሎ ያደረገ ሕዝብ ነው ብለዋል።ዋነኛው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መስመር የሆነውን የጂቡቲ ኮሪደርን የያዘው አፋር አበርክቶዎቹ ይበልጥ ከፍ እንዲሉ ከምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሕዝቦች ጋር ያለውን ቁርኝት የሚያሳድጉ አገር አቀፍ ስራዎች መከናወን እንዳለባቸው ሻለቃ መሃሪ ገልጸዋል።እንደ ሻለቃ መሃሪ ገለጻ፤ አፋር ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የምስራቅ አፍሪካን ቀጣና በኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና በባህል ስርዓቶች በማስተሳሰር ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ ህዝብ ነው።አፋሮች ከኢትዮጵያም አልፎ ከጎረቤት ሃገራት ጋር በባህልና በቋንቋ ሰፊ ማህበራዊ ቁርኝት ፈጥረው መኖርን ባህል አድርገውታል። በኢትዮጵያ ያሉ አፋሮች ከኤርትራና ከጂቡቲ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ከሚገኙ ዜጎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነታቸውን አጠናክረው በመቀጠል ረገድ ለሌላውም ዓርአያ የሚሆን ስራ እያከናወኑ ነው ብለዋል።ከዚህ ባለፈ በአገር ሽማግሌዎች፣ በሐይማኖት መሪዎችና አጠቃላይ ሕበረተሰቡን ባሳተፉ ባህላዊ ስርዓቶችን በመጠቀም የምስራቅ አፍሪካ አገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር እንዲሁም ቀጣናው የተረጋጋና ሰላማዊ እንዲሆን ሰፊ ስራ አከናውኗል ሲሉ ተናግረዋል።የሰው ልጅ ዝርያ መገኛና የበርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻ የሆነው አፋር የታማኝነት፣ አገርን በጽኑ የመውደድና እንግዳን የማክበር ትውፊቶቹን በማሳደግ ለአገራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ መደገፍ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።አፋሮች እንኳን እኛ ግመሎቻችንም የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ያውቁታል የሚል አባባል አላቸው። በእያንዳንዱ ስራቸው መሃል ለአገር አንድነት የመቆርቆር ስሜትን እያዳበሩ ያድጋሉ። ይህን ልምዳቸው ወደቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር በትምህርት ቤቶች አካባቢ ይበልጥ መስራት ይገባል ሲሉ ሻለቃ መሃሪ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።በተለይ ባህላዊ እሴቶቻቸውንና የአገር ፍቅር ስሜቶቻቸውን የሚያሳዩባቸውን መንገዶች፣ ለዕውነትና ለታማኝነት ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት እንዲሁም እንግዳ ተቀባይነታቸውን በተመለከተ ትውልዱ ይበልጥ እንዲገነዘበው ማድረግ ይገባል ብለዋል።ሻለቃ መሃሪ እንዳስታወቁት፤ ትውልዱ የአፋሮችን መስተጋብራዊ ትውፊትና ባህሎችን ጠንቅቆ እንዲያውቅ በመስራት ከኢትዮጵያ አንድነት ባለፈ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር መጠናከር የሚጠቅሙ እሴቶችን በዘላቂነት ማዳበር ይገባል።ጌትነት ተስፋማርያምአዲስ ዘመን  ታኅሣሥ 30 /2015Facebook    Instagram  Twitter  

No comments:

Post a Comment

<script async src="https://pagead2.googlesyndication.com/pagead/js/adsbygoogle.js?client=ca-pub-8211633838377135" crossori...